Statement from Oromo Federalist Congress: የታሪክ ሽሚያ ለማካሄድ ካልሆነ በስተቀር የእሬቻ ሰማዕታት ፓርክ/ሐዉልት በተጠያቂዎች ሊቆም አይገባም፤ በመሬት ጥያቄ ምክንያትም የሰዉ ሕይወት አይቀጠፍም፡፡ September 7, 2017
Posted by OromianEconomist in OFC, Uncategorized.Tags: Africa, Bishoftu Massacre 2nd October 2016 at Irreecha, Ethiopia, Genocide Against Oromo People, Janjaweed in Darfur Liyu Police in Oromia, ofc, Oromia, Oromo, Statement from Oromo Federalist Congress
trackback
የታሪክ ሽሚያ ለማካሄድ ካልሆነ በስተቀር የእሬቻ ሰማዕታት ፓርክ/ሐዉልት በተጠያቂዎች ሊቆም አይገባም፤ በመሬት ጥያቄ ምክንያትም የሰዉ ሕይወት አይቀጠፍም፡፡
ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ የተሰጠ መግለጫ
መስከረም 22 ቀን 2009 የእሬቻን ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓል ለማክበር በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በተሰባሰቡ የኦሮሞ ዜጎች ላይ ሆን ተብሎ በተወሰደ የመንግስት ያልተገባ እርምጃ የብዙ ዜጎች ሕይወት ተሰዉቷል፡፡ አስቀድሞ ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በመጠርጠር ፓርቲያችን፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ “የእሬቻ በዓል የሕዝብ ባህልና ሃይማኖት በጣምራ የሚከበርበት መሆኑ ታዉቆ ማናቸዉም የፖለቲካ ኃይሎች ከዋዜማዉ ጀምሮ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ አበክረን እናሳስባለን፡፡” የሚል መግለጫ መስከረም 10/2009 ማዉጣታችንን እናስታዉሳለን፡፡
የሰጠነዉ ማሳሰቢያ የመንግስት ባለሥልጣን ሰሚ ጆሮ ባለማግኘቱና ቀደም ሲልም በሕዝብና በገዥዉ ፓርቲ መሀከል የነበረዉ መልካም ያልሆነዉ ግንኙነት ፈጦ ሊወጣ በመቻሉ በተለይም ወጣቱ የተቃዉሞ ድምፅ በማሰማቱ የመንግስት ኃይሎች በታዘዙት መሠረት የኃይል እርምጃ ወስደዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ጥቂት በሚባሉ ወጣቶች የተቃዉሞ መፈክር ማንሳት የተነሳ፤ የመንግስት ኃይሎች ኃላፊነት በጎደለዉ ሁኔታ እጅግ ብዙ ሆኖ በተሰበሰበዉና ምንም ማምለጫ መንገድ በሌለዉ ንጹኃን ሕዝብ ላይ የኃይል እርምጃ ተወስዷል፡፡ በዚያ ዓይነት ሁኔታ በሕዝብ ላይ የበቀል እርምጃ መዉሰድ እጅጉን የሚከብድ መሆኑ ማመዛዘን ለሚችል ሰዉ የሚከብድ መሆኑ እየታወቀ፤ ከአቅም በላይ የሆነ እርምጃ በመወሰዱ የብዙ ዜጎቻችን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ አልፏል፡፡
የዚህ መግለጫ አስፈላጊነት ደግሞ እነዚያን በግፍ የተገደሉ ዜጎችን ለማስታወስ ሲባል የመታሰቢያ ፓርክ የሚባል ተገቢ ባልሆነ ቦታ ላይ ተገቢ ባልሆነ አካል መሰራቱ ነዉ፡፡ በወቅቱ የተገደሉ ዜጎች ተለይተዉ መላዉ ሕዝብ ባላወቀበትና በገለልተኛ አካል ተጣርቶ በኦሮሞ ሕዝብ ደንብ መሠረት ጉማ ወይም የደም ካሳ ባልተከፈበት ሁኔታ ዉስጥ ሆኖ፤ ገዳዮችና አዛዦቻቸዉ ለፍርድ ሳይቀርቡ ፓርክ ተሰራላቸዉ ሲባል የሟች ቤተሰቦችም ሆኑ መላዉ ሕብረተሰባችን የሚቀበሉት አይደለም፡፡ ምክንያቱ ቀላል ነዉ፡፡ የሰማዕታት ሐዉልትም ሆነ የመታሰቢያ ፓርክ በተጠያቂዎች አይገነባም፡፡ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስትም ሆነ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የሚጠበቅ ነገር ቢኖር የሟቾችን ማንነት በገለልተኛ አካል ይፋ ማድረግ፣ ጉማ ወይም የደም ካሳ መክፈልና ገዳዮችን ለፍርድ ማቅረብ ነዉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተሰራ የተባለዉ የመታሰቢያ ፓርክም ዜጎቹ ከተገደሉበት ቦታ ርቆ መተከሉ የግብር ይዉጣ ሥራ ከመሆኑም በላይ የታሪክ ሽሚያ ለማካሄድ ካልሆነ በስተቀር የእሬቻ የሰማዕታት ሐዉልትም ሆነ ፓርክ በተጠያቂዎች ሊቆም አይገባም እንላለን፡፡ በሌላም በኩል ሕብረተሰቡ እነዚህ የተሰዉ ወገኖች በጥልቅ ሐዘን የሚያስታዉሳቸዉ ከመሆኑም በላይ ስማቸዉንና ምስላቸዉን በዝርዝር ማስቀመጥ ሲገባ እንዲሁ አንድ ቁም ድንጋይ ተክሎ ከጉዳዩ ጋር የማይመስለዉን ሀተታ በጽሑፍ ማስቀመጡ አሳዝኖናል፡፡ ከዚህ ጋርም በፓርኩ የመግቢያ በር ላይ በአፋን ኦሮሞ ተጽፎ የሚገኘዉ “Paarkii Yaadannoo Namoota Ayyanaa Irreechaa Irratti Lubbuun Isaani Tasa Darbe Yaadachuuf Moggaafame” የሚለዉ ዜጎቹ የሞቱት በድንገተኛ ሁኔታ እንደሆነ በጽሑፍ ማስቀመጡ በኦሮሞ ዜጎች መስዋዕትነት ላይ የማፈዝ ያህል ስለሆነ ተጨማሪ የሕዝብና የመንግስት ግጭትን ሳይጋብዝ ከቦታዉ እንዲነሳ እንጠይቃለን፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከኦሮሚያ ክልል ላይ የድንበር ጥያቄ የሚያነሱና በድንበሮች አካባቢ በሚገኙ የኦሮሞ ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ኃይሎች ጉዳይ ከአሳሳቢ ደረጃም ያለፈና የዜጎቻችንን ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ይህ የመሬት ጥያቄ የድንበር አከባቢ ሕዝቦችን በማጋጨት ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት እያስከፈለ ይገኛል፡፡ የመሬት ጥያቄዉን አንዳንዴ ሲመለከቱት ኢትዮጵያዊያን በቀጣይ ጊዜያት ዉስጥ አብሮ የመኖር ዕጣ ፋንታቸዉ እያበቃ ያለ ያስመስላል፡፡ ምክንያቱም በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብና በምስራቅ ኦሮሚያ በኩል የሚገኙት የገዥዉ ፓርቲ ካድሬዎችና ካቢኔዎች የሕዝቦች አብሮነት እንዲያከትም ፍላጎት ያላቸዉ ይመስላሉ፡፡
በድንበር አከባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች በግጦሽ ሳር፣ በኩሬ ዉሃ፣ በጠፈ ከብትና በጥቃቅን ነገሮች ሊጋጩ እንደሚችሉና በአከባቢ ሽማግሌዎችና በጎሳ መሪዎች አማካይነት ሊታረቁ እንደሚችሉ፤ እነዚህ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች ችግሮችን ሲፈቱም እንደነበረ ይታወቃል፡፡ የመሬት ወረራዉና የሰዎች ግድያዉ የኦሮሞን ሕዝብ ቁጥርና የኦሮሚያን የቆዳ ስፋት ለማሳነስ ታቅዶ የተቀመጠዉን እስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ያለ ይመስላል፡፡ በተለይም በምስራቅ ኦሮሚያ በኩል በሱማሌ ልዩ ኃይል በኦሮሞ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለዉ ጥቃት እጅጉን ያሳስበናል፡፡
ስለሆነም እንደዚህ ዓይነት የጥቃት እርምጃዎች ለወደፊቱ ኢትዮጵያዊያን አብሮነት የማይፈይድና ወቅትን እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጂ እየሆነ ስለሚቀጥል የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላትና ሕብረተሰቡ አስፈላጊዉን የዕርምት እርምጃ እንዲወስዱ አበክረን እናሳስባለን፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ
ፊንፊኔ፤ ጳጉሜን 2/2009
Comments»
No comments yet — be the first.