Ethiopia: የህወሓቶች ቁጥር የበዛው የሌብነቱ ፈር-ቀዳጅ እና ፈቃጅ ስለነበሩ ነው! November 21, 2018
Posted by OromianEconomist in Uncategorized.Tags: Africa, Corruption, CORRUPTION CRACKDOWN, Ethiopia, Ethiopia: TPLF's corruption empire, The study of Evil, Tyranny
trackback
ላለፉት አመታት በከፍተኛ የሌብነትና ሙስና ተግባር የተሰማሩት በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናትና ኃላፊዎች፣ ከመንግስት እና ገዢው ፓርቲ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላቸው በተለያየ የግል ባለሃብቶችና ድርጅቶች፣ እንዲሁም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሰሩ ሰራተኞች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ መንግስታዊ መዋቅርና የተቋማት ሥራና አሰራር የተዘረጋው፣ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚመራው በህወሓት መሪነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ነው። ከህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የተለየ ወይም የሚቃወም ሰው የፖለቲካ ስልጣን ሊኖረው አይችልም።
ከህወሓት የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያለው ግለሰብ በተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ አንኳን ወደ አመራርነት መምጣት አይችልም። በመሆኑም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አባላትና አመራሮች በሙሉ የህወሓት የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ የበላይነትን የተቀበሉ እና የሚያገለግሉ ናቸው። ከህወሓት ጋር የቀረበ ግንኙነትና የጥቅም ትስስር የሌላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጪ ቢዝነስ ተቋማት ኢትዮጵያ ውስጥ በነፃነት መስራትና መንቀሳቀስ አይችሉም።

የህወሓት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንደ ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሁሉ በሙስና እና በህገ ወጥ ዘረፋ ተግባር ተሰማርተዋል። ሆኖም ግን ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሙስና እና ዘረፋ ተግባር የተሰማሩት በህወሓት ፍቃድ እና ይሁንታ ነው። ስለዚህ ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ያለ ህወሓት ፍቃድና ይሁንታ በዘረፋና ሌብነት ተግባር ውስጥ መሰማራት አይችሉም። ምክንያቱም የህወሓትን የበላይነት የሚቃወሙ ሰዎች እንኳን መስረቅ በሀገራቸው ሰርተው መብላት አይችሉም።
በተመሳሳይ የህወሓት የሙስና እና ዘረፋ ተግባር የሚቃወሙ እና የሚያጋልጡ ሰዎች በነፃነት መናገር፣ መፃፍና መደራጀት አይችሉም። ከዚህ በተጨማሪ ከህወሓት ጋር የጠበቀ የጥቅም ትስስር የሌላቸው ተቋማትና ድርጅቶች እንኳን በህገወጥ ተግባር በህጋዊ መንገድ መስራትና መንቀሳቀስ አይችሉም። የህወሓት የበላይነት እና ጭቆና የሚቃወሙ ሰዎች በመንግስት ተቋማት ውስጥ ቀርቶ በግል ተቋማት ውስጥ እንኳን ተቀጥረው መስራት አይችሉም።
በአጠቃላይ ባለፉት 27 አመታት ያለ ህወሓት እውቅና እና ፍቃድ በህገወጥ ዘረፋና ሙስና ተግባር የተሰማራ የመንግስት ባለስልጣን፣ የንግድ ድርጅት ወይም አገልግሎት ሰጪ ድርጅት የለም። በዚህ መሰረት የህወሓት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፎዎች በራሳቸው በሙስና እና ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ከመሰማራታቸው በተጨማሪ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የመንግስት እና የግል ሰራተኞች በዘረፋና ሌብነት ተግባር እንዲሰማሩ አድርገዋል። ስለዚህ የህወሓት አባላትና አመራሮች መጠየቅ በራሳቸው ለፈፀሙት ዘረፋና ሌብነት ብቻ ሳይሆን ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች፣ ተቋማት እና ሰራተኞች በተመሳሳይ ህገወጥ ተግባር እንዲሰማሩ ፈር-ቀዳጅ እና ፈቃጅ በመሆናቸው ጭምር ነው። ከዚህ አንፃር በህግ የሚጠየቁ የህወሓት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ቁጥር ከሌሎች አንፃር ሲታይ ብዙ ቢሆን ሊገርመን አይገባም።
Comments»
No comments yet — be the first.