jump to navigation

The Ethiopian Evangelical Church Mekane Yesus calls on the Fascist Ethiopia’s regime (TPLF) to reverse the state of emergency.የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ መልዕክት February 24, 2018

Posted by OromianEconomist in Uncategorized.
Tags: , , , , , , ,
trackback

Odaa Oromoooromianeconomist

The Ethiopian Evangelical Church

(ይህ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ መልዕክት ነው)

ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ መንግስት፤ የካቲት 15-2010 ዓ.ም
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤
ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ፤
ለሕዝበ-ምዕመናን በሙሉ፤
የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የቀረበ ጥሪ፤
እንደሚታወቀው፣ ቤተ ክርስቲያን ከነገድ ሁሉ፤ ከቋንቋም ሁሉ፣ ከወገንም ሁሉ፣ ከሕዝብም ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ የተዋጁ ምዕመናን አንድነት ናት፤ የእምነቷ መሠረት የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቤተክርስቲያንም ሆነች መንግስታት ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሕዝቡን በታማኝነትና በጽድቅ የማገልገል ታላቅ ኃላፊነትና አደራ በሚገባ መወጣት እንዳለባቸው በአጽንኦት ያስተምራል፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር የእግዚአብሔር መንግስት እንደራሴ እንደመሆኗ፤ ሕዝቦችም ሆኑ መንግስታት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በፈርሃ እግዚአብሔር በመልካም ሁኔታ እንዲወጡ የማስተማር፣ የመምከርና የማሳሰብ፣ ግዴታ አለባት፡፡
ይህን ታላቅ አደራ ከመወጣት አኳያ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ሁኔታዎችን ስታጤን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን ትገነዘባለች፤ ከሰብኣዊ መብት አያያዝ፣ ከዲሞክራሲ፣ ከፍትህ፣ እና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ አካባቢዎች በመንግስትና በህዝቡ መካከል የከረረ አለመግባባት መታየት ከጀመረ ውሎ ያደረ ሲሆን ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ደግሞ ህዝቡ፤ በተለይም ወጣቱ ትውልድ በሰላማዊ ሰልፍና አንዳንዴም ሀይል በተቀላቀለበት መልኩ ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞውን ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል፤ በእነዚህም እንቅስቃሴዎች መነሻነት በጸጥታ ሀይሎችና በህዝቡ መካከል በተፈጠሩ ተደጋጋሚ ግጭቶች እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፣ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ በርካታ ንብረቶችም ወድመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የህብረተሰቡ አካል እንደመሆኗ መጠን ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በተለያዩ ክልሎች መከሰት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ ፍትህ የሰፈነበት እርቅና ሰላም እንዲወርድ በጸሎት እግዚአብሔር አምላኳን ስትማጸን የቆየች ከመሆኑም በላይ መንግስት ህዝቡ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ተገቢና ፍትሃዊ ምላሽ በአፋጣኝ እንዲሰጥ፣ ህዝቡም ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያቀርብ ጥሪዋን በተናጠል፣ እንዲሁም ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ስታቀርብ ቆይታለች፤ መንግስትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሱን በመገምገምና የችግሮችን ምንጮች በመለየት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ ከመጠየቅም አልፎ በህዝቡ ጥያቄ መሠረት የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት መጀመሩ የሚያስግነው ነው፡፡ በቀጣይነትም፣ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ሁሉ የሀገር አንድነትና የሕዝቡ ሠላም ይበልጥ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲገነባ በጋራ መግባባት ላይ መስርቶ መሥራት ስለሚያስፈልግ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የሚከተለውን ጥሪ በከፍተኛ አክብሮትና በታላቅ ትህትና ታቀርባለች፡-
ሀ. ለኢፌዲሪ መንግስት
1. የማንኛውም መንግስት የህልውና ምንጭና መሰረት ሀገርና ሕዝቡ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም፤ ስለሆነም ገዢው ፓርቲም ሆነ የኢፌዲሪ መንግስት ከማንኛውም ፖለቲካዊ አስተሳሳቡም ሆነ እቅዱ ይልቅ ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝቡ ደህንነትና አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጥ፤
2. ኢትዮጵያ ሀገራችን ሰላሟ ተረጋግጦ እንድትቅጥል፣ ሕዝቦችዋም በአንድነትና በእኩልነት ተባብረውና ተጋግዘው በፍቅር የመኖር ነባር እሴታቸውን አጎልበተው እንዲቀጥሉ ለማድረግ የሚቻለው ሀገራዊ የጋራ መግባባት ሲኖር በመሆኑ፣ የተለያየ ግንዛቤና አመለካከት አለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች/ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ በማመቻቸት መንግስት ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤
3. ቤተክርስቲያኒቱ ሰሞኑን ሀገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር እንድትተዳደር መደረጉ የፈነጠቀውን የሠላምና የመግባባት ተስፋ አደብዝዞ ሀገሪቱን ይበልጥ አሳሳቢ በሆነ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊያስገባት ይችል ይሆን የሚል ሥጋት ስላሳደረባት፣
3.1 መንግስት ያሉትን ሁኔታዎች በጥልቀት አጢኖ ቢቻል አዋጁን ማንሳት በሚቻልበት መንገድ ላይ እንደገና እንዲመክር፤
3.2 አዋጁ ሥራ ላይ ይዋል ከተባለ ደግሞ በአፈጻጸሙ ወቅት የዜጎች መሰረታዊ መብትና ሰብዓዊ ክብር እንዳይነካ ብርቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ፤
4. መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የሃሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይትና ድርድር ለማስተናገድ እንዲሁም ከፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ የታሰሩትን እስረኞች በመፍታት ለሕዝቡ ጥያቄ መስጠት የጀመረውን ተግባራዊ ምላሽ አጠናክሮ እንዲቀጥል፤
ለ. ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች
1. ከላይ በተራ ቁጥር ሀ.1 እንደተጠቀሰው፣ የግልም ሆነ የቡድን ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችን በነጻነት ለማራመድና ተወዳድሮ በማሸነፍና በመሸነፍ ሥርዓት ውስጥ ውጤታማ መሆን የሚቻለው ሀገርና ሕዝብ ሲኖር እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም፤ ስለሆነም ሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገሪቱ አሁን ከገባችበት ችግር እንድትወጣ ከየራሳቸው መርህና ፍላጎት ይልቅ ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝቡ ደህንነትና አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጡ፤
2. የሃሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይትና በድርድር የማራመድ፣ ለጋራ መግባባትና ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያደርጉና ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ፤

ሐ. ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ
1. መላው የሃገራችን ሕዝቦች በተለይም ወጣቱ ትውልድ ነገ የሚረከባት ሀገር የተጎሳቆለች እንዳትሆን፣ ያለውን ጥያቄ ሁሉ በከፍተኛ የሀላፊነት ስሜትና የዜግነት ዲሲፕሊን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያቀርብ፣ በተጨማሪም አሁን መንግስት በተለያዩ ዘርፎች እየወሰደ ያለውን የለውጥ ርምጃ በትዕግስት እንዲከታተል፣ ሁከት ተስፋፍቶ በሀገሪቱ ያለዉ ውጥረት እንዳይባባስ ብርቱ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፤
2. አሁን አልፎ አልፎ የሚታዩት ብሄር-ተኮር ግጭቶች አደገኛ አዝማሚያ ስለሆኑ፤ ከጥንት ጀምሮ የቆየው አብሮነት፣ ተግባብቶና ተጋግዞ በፍቅር የመኖርን አኩሪ ኢትዮጵያዊ እሴት/ባህል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንዲያዳብረውና እንደ ዓይኑ ብሌን እንዲጠብቅ፤

መ. ለመላው ሕዝበ-ምዕመናን
እኛ፣ የብዙ ብሄር-ብሄረሰቦች እናት የሆነችው ኢትዮጵያ ሀገራችን በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብትሆን ጠባቂና ታዳጊዋ ልዑል እግዚአብሔር እንደሆነ በጽኑ እናምናለን፤ በመሆኑም፡-
1. በሀገራችን ፍርድ እንደ ውኃ ፅድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ እስኪሆን ድረስ ምዕመናን ሁሉ በትጋት በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን እንዲማጸኑ፤(2ዜና 7፡14፣ አሞ. 5፡24)
2. ምዕመናን ሁሉ የምድር ጨው፣ የዓለም ብርሃን፣ እንዲሁም የሰላም መልዕክተኞች እንደመሆናቸው፣ የማስታረቅ ተልዕኮአቸውን እንዲወጡ፤ (ማቴ 5፡13-16)
3. ምዕመናን ክርስቲያናዊ የዜግነት ግዴታቸውን በየተሰማሩበት መስክ በመወጣት ክርስቲያናዊ አርአያነታቸውን እንዲያሳዩ፤
ቤተክርስቲያን ጥሪዋን በአጽንኦት ታስተላልፋለች፡፡
ስለዚህ ከላይ ጥሪ የተደረገላችሁ አካላት በሙሉ እንዲሁም ሲቪል ማህበራትና የሀገር ሽማግሌዎች ለዚህ ብርቱ ሀገራዊ ጉዳይ ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ በመስጠት እንድትመክሩበት፣ በኢትዮጵያዊ የመቻቻል መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ የሚሊዮኖች የጋራ መኖሪያ የሆነችውን ውድ ሀገራችንን ከተጋረጠባት አደጋ እንድትታደጉ ቤተክርስቲያኒቱ ከአደራ ጭምር ጥሪዋን በትህትና ታስተላልፋለች፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን፣
ሃገራችንን ይባርክ፣ ይጠብቅ፣
ፊቱንም ያብራላት፣ ጸጋውንም ያብዛላት፣
ፊቱን ይመልስላት፣ ሰላሙንም አብዝቶ ይስጣት፡፡
አሜን!

Comments»

No comments yet — be the first.

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: